ሀምሌ 20/2018 ዓ.ም (ኢ.ደ.ል)
************************®*********************
የኢትዮጵያ ደን ልማት ተቋም ከክልል ባለድርሻዎች ጋር የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅና መናበብ የውይይት መድረክ አካሄደ፡፡
ሀገራዊ የአስር አመታት መሪ ዕቅድን መነሻ በማድረግ ደን ዘርፍ የመካከለኛ ዘመን እቅድ ላለፉት ሶስት ዓመታት ሲተገበር የቆየ ሲሆን ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በደን ዘርፍ ለማሳካት የተጣሉና በደን ልማት፤ በደን ጥበቃና እንክብካቤ፤ በደን ውጤቶች ግብይትና በዘርፉ ከሚከናወኑ የምርምር ተልዕኮዎች በስኬታማነት እየተተገበሩ ቆይተዋል፤ ስኬትም ተመዝግቧል፡፡
በዚሁ ማዕቀፍ መሰረት የዘርፉ ያለፈው በጅት ዓመት በተለዩ 12 ግቦች ተለይቶና ዒላማ ተቀምጦ ሲተገበር የቆየ ሲሆን ተቋሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን “የአንድ እቅድ አንድ ሪፖርት“ ስርዐት በመከተል እንደየ ክልሎች ነባራዊ ሁኔታና ፖቴንሺያል በመናበብ በጋራ መስራት በመቻሉ ስኬታማ ውጤትን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
በዚሁ መሰረት በክልሎች የተደራጁ የአካባቢ ጥበቃ፣ የአካባቢ፣ ደንና ዓየር ንብረት ለውጥ፤ የደን ኢንተርፕራይዞች፤ የደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ፤ የግብርና ቢሮዎች፤ የግብርናና የገጠር መሬት አስተዳዳር እንዲሁም ተዛማጅ የሆኑ ባለድርሻ ተቋማት የዘርፉን ዕቅድ አፈፃፀማቸውንና የቀጣይ በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ አቅርበዋል፡፡
በሪፖርታቸውም ከታዩ ስኬታማ ውጤቶች መካከል በኦሮሚያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከደንና ዱር እንስሳት ውጤቶች ሮያሊቲ ብር 184.31 ሚሊዮን ማሰባሰብ መቻሉ፤ ከአጋር ድርጅቶች 2.7 ሚሊዮን ብር የልማት ድጋፍ ማሰባሰብ መቻሉ፤ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት በ5.09ሚሊዮን ቶን እኩሌታ መቀነስ መቻሉ፤ በደን ህግ ተከባሪነት ላይ ለ2.4 ሚሊዮን የማህበረሰብ አካላት ግንዛቤ ማስጨበጥ መቻሉ፤ በደን ዘርፍ ለ37,250 ሴቶችና ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩ እንደ ጥንካሬ ተወስደዋል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ ተራራ ልማት፣ 3.1 ቢሊዮን ችግኞችን በእስካሁኑ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ መተከሉና ጂኦ ሎኬትድ ሆና መያዙ፣ የተራራ እርከንና ፊዚካል ስትራክቸር መሠራቱ በአዎንታዊነት ሲታዩ በአማራ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ለበርካታ በእጣንና ሙጫ ኢንቨስትመንት ለመሠማራት ለጠየቁ ፍቃድ መሠጠቱና ሀብቱ ተሰብስቦ ለጥቅም እንዲውል መደረጉ፤ ከልማት አጋር አካላት የሚገኙ የሀብት ድጋፎችን በመንግስት ከሚመደብ ሀብት ጋር በማጣጣምና በመናበብ ውጤታማ ስራ መሠራቱ፤ በአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች አበረታች ውጤት ማምጣት፣ ለወጣቶችና ለሴቶች በዘርፉ የስራ እድል እንዲፈጠር ማድረግ በበጎነት የተነሱ ሲሆን በአማራ ደን ኢንተርፕራይዝም በሀብት ማሳደግ፣ በዛፍ ዘር አሰባሰብ፣ በደን ችግኞች ፅድቀት መጠን ማሻሻል፣ በስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዙ ከሚሰራቸው ስራዎች ማህበረሰቡ በየደረጃው ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ በክልሉ የሚገኘውን ከፍተኛ የተፈጥሮ ደን ጠብቆ በማቆየት፣ 777 ሺህ ሄክታር ደን በ600 ማህበራት የአሳታፊ ደን አስተዳደር ስርአት ስር በማስገባት የደን ጥበቃንና የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን በዘላቂነት ስርዐት መዘርጋት መቻሉ፤ ሀገር በቀል የደን ዝርያዎች እንዲጠበቁና እንዲስፋፉ እየተሰራ መሆኑ፤ ወደ ክልሉ በደን ዘርፍ የሚመጡ ኢንቨስትመንቶችና የድጋፍ ሀብቶችን ከመንግስት ሀብት ጋር አጣጥመው ለልማት ማዋላቸው በበጎ ተሞክሮነት የተነሱ ሲሆን በደቡብ ኢትዮጵያ ግብርና ቢሮ በኩል ግለሰብ ዜጎች የችግኝ ማፍላትና ጥቅም ሊይ ማዋል ልምድ እየጨመረ መምጣት፣ የተራራ ልማት፣ ከተከላ በፊት የደን ችግኝ ተከላ ቦታዎችን በአግባቡ መለየት፣ መከልና ደረጃውን የጠበቀ ጉድጓድ አዘጋጅቶ መትከል እንዲሁም ችግኞችን በየፋይዳቸውና እንደየ ስርዐተ ምዳራቸው ለይቶ መትከል በጥሩ ተግባርነት ተገልፀዋል። በሲዳማ ክልልና አዲስ አበባ አስተዳደርም በርካታ የተሰሩ ስራዎች ቀርበው የጋራ ምክክርና ልምድ ልውውጥ ተካሂዷል።
በመጨረሻም ከቤቱ በርካታ ጥያቄዎች፣ ማብራሪያዎችና ምላሾች እንዲሁም የቀጣይ ስራዎች አፈፃፀም አቅጣጫና የስራ አመራር በተቋሙ ዋና ዳይሬክተር በክቡር አቶ ከበደ ይማም ተሰጥቶ መድረኩ ተጠናቋል።




