ሀምሌ 27/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ
****************®************
የኢትዮጵያ ደን ልማት አመራሮችና ሠራተኞች “ተስፋን እንትከል!!” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ከተማ በቦሌ አራብሳ ቂርቆስ አደባባይ አካፋይ ዛሬ ማለዳ የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ አካሄዱ፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ በተደራጀ የህዝብ ተሳትፎና ንቅናቄ ከ48 ቢለዮን በላይ የተለያየ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች መትከል ተችሏል፡፡ በያዝነው የክረምት ወራትም 8 ቢሊዮን ችግኞችን የመትክል ስራ እየተከናወነ ሲሆን በአንድ ጅምበር 8 መቶ ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ደን ልማት አመራሮችና ሠራተኞች “ተስፋን እንትከል!!” በሚል መሪ ሀሳብ የአንድ ጀንበር የሀገር በቀል ችግኝ ዝርያዎችን ተከላ ያካሄዱ ሲሆን እነዚህ ዝርያዎች ለከተማ ውበት የተመረጡ ናቸው።
በተከላ ፕርግራሙ ማስጀመሪያ ላይ ስለ ችግኝ አተካከል ቅደም ተከተልና መከተል ስለሚኖርባቸው መስፈርቶች ለሠራተኞች ገለፃ ተደርጓል። ገለፃውን የሰጡት በኢትዮጵያ ደን ልማት የአረንጓዴ አሻራና ሰው ሰራሽ ደን መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ አበሩ ጠና ሲሆኑ መሪ ስራ አስፈፃሚው በገለፃቸው “ለችግኞች ፅድቀትና እድገት የአተካከልና ከተከላ በኋላ የሚደረገው እንክብካቤ ወሳኝ ነው” ብለዋል።
የአቶ አበሩን ገለፃ ተከትሎ የእለቱን ተከላ ያስጀመሩት በተቋሙ የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተሾመ ዘውዴ እንዳሉት “የኢትዮጵያ ደን ልማት አመራሮችና ሠራተኞች የአረንጓዴ አሻራ የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ ላለፉት ሰባት አመታት በውጤታማነት ሲተገብሩ መቆየታቸው ይህ ሀገርን በልማት ለማገልገል ትውልዶች በብዙ ትውልዶች መካከል አልፎ አልፎ የሚገኝ እድል ነው” ብለዋል።
የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ የበአመቱ በሚከናወነው የክረምት ወራት እኩሌታ የሚከናወን ሲሆን በመላ ሀገራችን እስካሁን ከተያዘው እቅድ አንፃር እቅዱን ለማሳካት በሚያስችል ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል።
የአንድ ቀን የአረንጓዴ አሻራ ብሄራዊ መርሀ ግብር ከማሳካት አኳያ በመላ ሀገራችን ህዝቡ ርብርብ እያደረገ ሲሆን እስከ ቀን እኩሌታ ድረስም 578.6 የተለያየ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች ተተክለዋል።



