የዓለምን እርቃን እየሸፈነች ያለችው ኢትዮጵያ!

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ****************®************** ዓለም በረጅም ዓመታት ዝግመተ ለውጥና ቁጥጥር ባጣ የሰው ልጅ እንቅስቃሴ ምክንያት የአረንጓዴነት ውበቷን እጥታለች።
ለእርሻ፣ ለእንጨት ምርትና ለከተሞች መስፋፋት ሲባል የተካሄደው የደን ጭፍጨፋ የምድራችንን የተፈጥሮ ሚዛን በማዛባት አስቀድሞ የነበረውን የ57 በመቶ የደን ሽፋን ወደ 31 በመቶ ዝቅ አድርጎታል።
እንደ ተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) መረጃ፥ በፈረንጆቹ 1990ዎቹ በየዓመቱ በአማካይ 10 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር ደን ይጨፈጨፍ ነበር።
ከ2015 እስከ 2025 ባሉት ዓመታት ይህ ቁጥር ወደ 4 ነጥብ 12 ሚሊዮን ሄክታር ዝቅ ማለቱ አዎንታዊ ለውጥ ያሳየ ቢሆንም፤ አሁንም በየዓመቱ የሚደርሰው አጠቃላይ የደን ውድመት አሳሳቢ ነው።
በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ሀገራት ወደ አየር የሚለቁት በካይ ጋዝ ከደን ውድመት ጋር ተደማምሮ ዓለምን ለከፋ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ለድርቅ፣ ለጎርፍና ለተዘበራረቀ የተፈጥሮ አደጋ ዳርጓታል።
በዚህ ቀውስ በካይ ጋዝ የማያመነጩ አዳጊ ሀገራት የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል።
ዓለም ዓመታዊ ጉባኤዎችን በመደጋገምና መሬት የማይወርዱ ቀቢጸ-ተስፋ ሀሳቦችን በማንሸራሸር ጊዜ ሲያባክን፤ ኢትዮጵያ ግን በተግባር የሚገኝ መፍትሔን ይዛ ብቅ ብላለች፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር።
በዚህ መርሐ ግብር ሀገሪቱ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ ሳይቋረጥ ችግኞችን በመትከል የተራቆቱ አከባቢዎችን በአረንጓዴ አልብሳለች።
አሀዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የዘንድሮን ሳይጨምር ባለፉት ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያ ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞችን ተክላለች።
በዚህም በ2010 ዓ.ም 17 ነጥብ 2 በመቶ የነበረውን የሀገሪቱ የደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ በማሳደግ የዓለምን እርቃን ለመሸፈን ትልቅ ድርሻ ተጫውታለች።
በተጨማሪም የውኃና አፈር ጥበቃ ሥራዎች የከርሰ ምድርና የገጽታ ውኃ ሀብት እንዲያንሰራራ በማድረግ የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቀነስ አስተዋጽኦ አድርጋለች።
ኢትዮጵያ ለራሷ ያዘጋጀችው ይህ መፍትሔ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትን አግኝቷል።
ይህን ታላቅ ቁርጠኝነትና የነባራዊ ለውጥ ውጤት በመገንዘብ ሀገሪቱ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (ኮፕ-32) እንድታዘጋጅ መመረጧ ለወሰደችው ተግባራዊ ርምጃ የተሰጠ ዓለም አቀፍ እውቅና ነው።
ኢትዮጵያ የጀመረችው ይህ አረንጓዴ ጉዞ ንግግር በበዛበት ዓለም ውስጥ በተግባር የተረጋገጠ መፍትሔ በመሆኑ፤ ምድሪቱን ከጥፋት ለመታደግ አማራጭ የሌለው የተቀደሰ ተግባር ሆኖ ቀጥሏል።

Related posts