ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር አህጉራዊ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያግዝ ነው ….

https://www.ena.et/web/amh/w/amh_3030442

ኢዜአ አማርኛ (https://www.ena.et/web/amh/w/amh_3030442)

አዲስ አበባ ሰኔ 30/2015 (ኢዜአ)

ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር አህጉራዊ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስርዓትን ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም ተናገሩ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አነሳሽነት የተጀመረው አገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ጅማሮውን ሐምሌ 2011 ዓ.ም አምስተኛ ዓመታትን አስቆጥሯል። በመጀመሪያው ምዕራፍም በአራት ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኝ የመትከል ዓላማን በማንገብ በአገር አቀፍ ደረጃ ከዕቅድ በላይ ከ25 ቢሊዮን በላይ የተለያዩ የእጽዋት ችግኞች መተከላቸው ይታወሳል።

በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ”ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ሃሳብ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በተያዘው ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተራቆተ መሬት በእጽዋት እንዲሸፈን በማድረግ የአየር ሚዛንን ለመጠበቅ መፍትሔ እያመጣ እንደሚገኝ በትላንትናው እለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያቸው ገልጸዋል።

አገር አቀፉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርም አገራቸውን ለመለወጥ ጉልበትና ገንዘባቸውን ፈሰስ እያደረጉ በሚገኙ ትጉ ኢትዮጵያዊያን እየተከወነ የሚገኝ ቀና ተግባር መሆኑን ተናግረዋል። በመርሃ-ግብሩ ለመድኃኒትነት የሚውሉ አገር በቀል ዛፎችን ጨምሮ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው እጽዋቶች እየተተከሉ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ መርሃ-ግብሩንም ኢትዮጵያውያን በላባቸው ተግተው እያሳኩት የሚገኝ አንጸባራቂ ድል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም ለኢዜአ እንዳሉት የአካባቢ የደን ሽፋን እየተራቆተ መምጣት ለዓለማችን እጅጉን ፈታኝና አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል። በአካባቢ መራቆት ሳቢያ ዓለምን እየፈተናት የሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥም ሊድንና ሊታከም የሚችለው በተፈጥሯዊ መንገድ በሚከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ የልማት ስራዎች እንደሆነ ገልጸዋል።

የመሪዎችን ከፍተኛ ቁርጠኝነት የሚጠይቀው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተካለ መርሃ ግብርም እጽዋትን በመትከል የደን ሽፋንን ለማሳደግ አይነተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን በማስተባበር ዘላቂና አስተማማኝ የኢኮኖሚ ለመገንባት የሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም የአየር ንብረት ለውጥን ምላሽ ለመስጠት ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

በሃምሳ ዓመታት ውስጥ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመዋጋት ታላላቅ ውሳኔዎችን ማሳለፍ ያስቻለ ዓለም አቀፍ ምክክር ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። ከውሳኔ ሃሳቡ ባሻገርም የአረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ስርዓት እንዲኖር ማድረግ የሚያስችል የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና አያያዝ ባህልን ማጎልበት አስፈላጊ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ የአየር ሚዛንን ለመጠበቅ እያካሄደች የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ ልማትም የአፍሪካ 2063 አጀንዳ ለማሳካት መሰረት የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል።

በአህጉረ አፍሪካ ከተራቆተው 100 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ ኢትዮጵያ 22 ሚሊዮን የሚሆነውን የተራቆተ መሬት በደን ለመሸፈን እየሰራች መሆኑን በአዎንታ አንስተዋል። ኢትዮጵያ የወሰደችው ተነሳሽነትም አህጉራዊ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስርአትን ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመላክተዋል። የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስራም ዓለምን ስጋት ውስጥ እየከተታት ለሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ዘላቂ መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል። የመሬት መራቆትን በመጠበቅ አስተማማኝ የአየር ሚዛን እንዲኖር ለማድረግም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን አጠናክሮ ማስቀጠል ሁነኛ አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል።

Related posts