(ወቅታዊ መልዕክት) 12 ጥር 2012: ደን በተለያዩ ነገሮች ተፅዕኖ ሊደርስበት ይችላል፡፡ በአለም ዙሪያ ከፍተኛ ችግር ከሚያደርሱ ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው ደግሞ የሰደድ እሳት ነው፡፡
በአለም ደረጃ በየዓመቱ በሰደድ እሳት በብዙ ሺህ ሄክታር የሚደርስ ደን የሚወድም ሲሆን በኢትዮጵያም እሰከ መቶ ሺህ ሄክታር ደን ላይ ጉዳት እንደሚደርስ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የቃጠሎው መንስዔ የተለያየ ቢሆንም በኢትዮጵያ በአብዛኛው ሰው ሰራሽ ችግር ነው፡፡ ሰዎች የእርሻ ማሳቸውን ለማዘጋጀት በሚያደርጉት የማቃጠል ሂደት እና በጫካ ማር ቆረጣ ሂደት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንደሆኑ የተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡
በኢትዮጵያ ከጥር እስከ መጋቢት ባሉት ነፋሻማና ሞቃት የአየር ሁኔታ በሚጠናከርበት ወቅት የደን ቃጠሎ በብዛት ይከሰታል፡፡ በሃገራችን በሚከሰቱ የደን ቃጠሎዎች የሰውና ቤት እንስሳትን ከመቅጠፍ ጀምሮ እስከ ብርቅዬ የሆኑ የዱር እንስሳትን መግደል እና እንዲሰደዱ ምክንያት በመሆን ከፍተኛ ጥፋት ከማድረሱም ባሻገር በአካባቢው ላይ ሥነ ምህዳራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ያስከትላል፡፡
በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የደን ቃጠሎ በአለም ላይ ካለው የሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱንና ለመከላከል አዳጋች እየሆነ መምጣቱ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ለዚህም ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ በሰሜን ብሄራዊ ፓረክ እንዲሁም በቅርቡ በአውስትራሊያ የተከሰቱት የደን ቃጠሎዎች ትልቅ ማሳያ ናቸው፡፡
ስለሆነም በተለይ ከላይ በተገለፁት ደረቅና ሞቃታማ ወቅቶች በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሰደድ እሳት እንዳይከሰት አርሶ አደሩ፣ የደን ባለሙያውና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የነቃ ክትትልና ቁጥጥር ሊያደርጉ ይገባል፡፡