ጥር 7 ቀን 2012 አዲስ አበባ:- ዛፍን በመትከል አለማችንን የተሻለች በማድረግ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማምጣት ይቻላል፡፡ ዛፍን በአግባቡ ከያዝነው ቁሳቁስና የተለያዩ ግልጋሎቶችን በመስጠት ከፍተኛ ጠቀሜታይሰጠናል፡፡ ዛፍ ከጠፋ ቀጣይነት ያለው ህይወት ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ የዛፎች መኖር የህልውና ዋስተና ናቸው፡፡ ደን ሊሻሻል፣ ሊያድግ እና ሊጠበቅ የሚችል ታዳሽ የሆነ ሃብታችን ነው፡፡ ዓለምን የተሻለች ለማድረግና ለማስቀጠል ዛፍን እንደመትከልና መንከባከብ የመሰለ አስደሳችና ቀላል ዘዴ የለም፡፡
በ1992 በተደረገው የመሬት ጉባኤ (Earth Summit) ብዝሀ ሕይወት፤ የአየር ንብረት ለውጥና በረሃማነት ጉዳይ ጀምሮ ስለደን በተደጋጋሚ ትኩረት እንዲሰጠው የተወሰነ ሲሆን በተለይ በ2012 በተደረገው የሪዮ ስብሰባ የዓለም መንግስታት የተቀናጀ የዘላቂ ልማት በኢኮኖሚ በማህበራዊ እና በአካባቢያዊ ዘርፎች እንዲረጋገጥ ስምምነት ተደርሷል፡፡ አለማችን በቀጣይ በምንፈልጋት መልኩ እንድትጠቅመን ዋና ዋና የሆኑትን የረሃብ፤ የጤና እና የአየር ንብረት ለውጥ የመሳሰሉ የአለማችን ችግሮች ለመቋቋም የአካባቢያችን ስነምህዳር መጠበቅ እንደዋናነት የተወሰደ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ስምምነት ሰነድ ላይ ለእነዚህ ችግር መፍተሄዎች እውቅና የተሰጠው የደን ልማቱ ነበር፡፡ የደን መመንጠርንና መራቆትን ለመከላከል የሚደረግ ጥረት እንዲጠናከር ትኩረት ያገኘ ርዕሰ ጉዳይም ነበር፡፡
የደን ልማት ትኩረት የዘላቂ ልማት እቅድና አተገባበር በሚገመገመው የአባል ሃገራት ስብሰባ በየዓመቱ ሲደረግ ስለ ደን ትኩረት ተሰጥቶ ልማቱ እንዲጠናከር ሳያሳስብ ቀርቶ አያውቅም፡፡ ውሳኔዎቹን ተከትሎ ብዙ ስራዎች ቢሰሩም አሁንም ግን የአለም ማህበረሰብ በጋራም ሆነ በተናጠል ለደን ልማት ትኩረት ተሰጥቶ ተጨማሪ ስራዎች መስራት ይጠበቅበታል የሚል አቋም ተይዟል፡፡ ይሄንን ተከትሎ የአለም መንግስታት በ2030 ለመድረስ የታቀደው 17 የዘላቂ የልማት ግቦችን ቀርፀው እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ከእነዚህ ግቦችም 10 የሚሆኑት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከደን ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ይህ የሚያሳየው የደን ልማትና ጥበቃው ምን ያህል ለዓለም ሀገራትም ሆነ ለሀገራችን ወሰኝ ሚና እንዳለው ነው፡፡
አንድ ሀገር ደንን በማልማት የከርሰ ምድር ውሃን በአስተማማኝ ደረጃ ለማግኘት፤ የአካባቢውን ስነ ምህዳር በመጠበቅ ምርታማነትን ለማሳደግና ወደ አካባቢ የሚለቀቀውን የካርቦንዳይኦክሳይድ መጠን በመቀነስ ንፁህ አየር ለማግኘት ይረዳል፡፡ በጥቅሉ ደን ለሰውል ጆችም ሆነ ለእንስሳት የህልውና መሰረት ነው፡፡
ዓለማችን ባለፉት ጥቂት ዓመታት አስተናግዳው የማታውቀውን ሙቀታማነትና ተደጋጋሚ ድርቅ ጉዳይ እንዲባባስ ያደረገው የሙቀት አማቂ ጋዞች መጨመር ነው ፡፡ ለዚህ ጋዝ መጨመር ደግሞ የደን መጨፍጨፍ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ በሀገራችን የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው በየዓመቱ ከደን መጨፍጨፍ 20 ሚሊዮን ሜተሪክቶን የሙቀት አማቂ ጋዝ ወደ አየር ይለቀቃል፡፡
አብዛኛው መሬቷ ተራራማ ለሆነው እና በዝናብ ግብርና ኢኮኖሚ ጥገኛ ለሆነችው ሃገራችን የደን ልማትን ማጠናከር ለነገ ሊባል የማይችል ተግባር ነው፡፡ኢትዮጵያ የደን ልማትን ለማጠናከር ካላት ቁርጠኝነት ተነስታ በአካባቢና ደን ላይ የሚሰሩ መስሪያ ቤቶችንና የምርምር ተቋማትን አቋቁማ እና የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፃ በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡
ይህን ቁርጠኝነት የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ በማውጣት ለደን ልማት የሚሆኑ ቦታዎችን በመለየትና አብዛኛውን ተራራ ላይ እርሻን በማስቀረት የግብርና ምርታችን በማሳደግ፤ የቱሪዝም ስራችን በማጠናከርና በረሃማነትን ለመከላከል ደን ልማት የህልውና ጉዳይ ተደርጎ በሁሉም ባለድርሻዎች በኩል ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት የሚገባ ዘርፍ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ማህበረሰቡ የደንን ጠቀሜታ እየተረዳ በመምጣቱ ለሚኖርበት አካባቢ ምቹና በአጭር ጊዜ ውስጥ ቶሎ ጥቅም ሊሰጡ የሚችሉ የዛፍ ዝርያዎች እንዲቀርብለት ፍላጎቱን በማሳየት ላይ ይገኛል፡፡ ይህን ተከትሎ ኢንስቲትዩታችን በሠራቸው የምርምር ሥራዎች የተለያዩ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር ዝርያ የሆኑ በምርምር የተለዩ የዛፍ ዝርያዎችን ቴክኖሎጂ በማውጣት ለተጠቃሚዎች ለማድረስና ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
በመሆኑም የተጀመረውን የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግና የእድገቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ለደን ልማቱ ትኩረት በመስጠት እየተከሰተ ያለውን የውሃ እጥረት፤ የምርታማነት መቀነስ፣ የጤና ችግሮች እና የሙቀት የመጨመረን መከላከል ይገባናል፡፡