በኢትዮጵያ እተተገበረ ያለው አሳታፊ የደን አስተዳደር ለምግብ ዋስትና፣ ለተለያዩ የገቢ ምንጮች፣ ለጠንካራ ኑሮ እና ለዘላቂ ደን ልማት አስተዋፆኦ እያበረከተ መሆኑ በጥናት መረጋገጡ ተገለፀ፡፡
አሳታፊ የደን አስተዳደር ለአካባቢው ማኅበረሰብ የደን ባለቤትነትና የማስተዳደር መብት በመስጠት ማኅበረሰቡ የተፈጥሮ ማር፣ የዱር ቡና እና ቅመማ ቅመሞ የመሳሰሉ ጠቃሚ የደን ምርቶችን አምርቶ ለገበያ እንዲያቀርቡ በማስቻል የገቢ ምንጮችን እያሰፋ ይገኛል። ይህ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ማኅበረሰቡ እንደ ድርቅ ያሉ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎችን እንዲቋቋም በማድረግ ጠንካራ ኑሮን ይገነባል።
የማኅበረሰቡን ደህንነት ከደኑ ጤናማነት ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ሥርዓቱ ዘላቂና አስተማማኝ የሆነ የደን ልማትና ጥበቃ ሥራን ያረጋግጣል።
በኢትዮጵያ አሳታፊ የደን አስተዳደር ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ወደ ሥራ የገባ ስትራቴጂካዊ አካሄድ ነው። ይህ ሥርዓት ቀደም ሲል የነበረውን ደኖችን ከማኅበረሰቡ አርቆ በመንግሥት ብቻ የመጠበቅ ልማድ በመቀየር በደን አቅራቢያ የሚኖሩ የአካባቢው ማኅበረሰቦች በውሳኔ ሰጪነት፣በባለቤትነት እና በተጠቃሚነት እንዲሳተፉ አድርጓል፡፡
በኢትዮጵያ በ1996 ዓ.ም ከ400,000 ሄክታር የነበረው የአሳታፊ ደን አስተዳደር በአሁኑ ጊዜ 3 ሚሊዮን ሄክታር መድረሱን በጥናቱ ተመላክቷል፡፡
በኢትዮጵያ ደን ልማት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ የደን ልማትና ምርምር ማዕከል የፖሊሲና ሶሾዮ- ኢኮኖሚክስ ዳይሬክቶሬት ተመራማሪ የሆኑት አቶ ጎንቼ ግርማ በመደበኛው “የምርምር-ለልማት” ሲምፖዚየም ላይ ባቀረቡት “አሳታፊ የደን አስተዳደር በኢትዮጵያ መጠቀም ለምግብ ዋስትና፣ ለተለያዩ የገቢ ምንጮች፣ ለጠንካራ ኑሮ እና ለዘላቂ ደን ልማት” አስመልክተው ባቀረቡት የጥናት ውጤትና ተሞክሯቸውን ለባለሙያዎችና ለተመራማሪዎች አካፍለዋል፡
ጥናቱ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በሲዳማ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ የአሳተፊ ደን ማህበራት ላይ የተሰራ መሆኑን የገለፁት አቶ ጎንቼ “በአሳታፊ ደን አስተዳደር የታቀፉ የደን ይዞታዎች በአሳታፊ ደን ካልታቀፉት ጋር ሲነፃፀር በደን ጥበቃ፣የገቢ አማራጭ ከማስፋት፣ የማህበራዊ ካፒታል ከማጠናከር እና የአረንጓዴ ባህልን ከማጠናከር አኳያ የተሻሉ እንደሆኑ” አስረድተዋል፡፡
