የኢትዮጵያ ደን ልማት በኦስትሪያ ከቦኩ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከ2023 ጀምሮ እያከናወነ ያለውን የሃበሻ ጥድን በቁርጥራጭ (Cuttings) የማባዛት ዘዴን በተመለከተ ለባለድርሻዎች ስልጠና ተሰጠ።
በቁርጥራጭ የማባዛት ዘዴ ዘር ለማግኘት አስቸጋሪ ለሆኑ፣የመብቀል አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ እና ለማደግ ረጅም ጊዜ ለሚወስዱ ሀገር በቀል የዛፍ ዝርያዎች ዘርን ሳይጠብቁ ዓመቱን ሙሉ በፍጥነት እና በብዛት ችግኝ ለማፍራት ያስችላል። በተጨማሪም የእናት ተክልን ጥሩ ባህሪያት ሳይለወጡ በትክክል ወርሰው እንዲያድጉ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ውድ የሆኑ የላቦራቶሪ ቴክኖሎጂ ሳይጠይቅ በአነስተኛ ወጪ ለአደጋ የተጋለጡ ብርቅዬ ዝርያዎችን ከጥፋት ለመታደግና ደኖችን መልሶ ለማገግም ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል።
በኢትዮጵያ ደን ልማት ከኦስትሪያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከ2023 ጀምሮ እያከናወነ ያለውን በቁርጥራጭ (Cuttings) የማባዛት ዘዴ የሃበሻ ጥድ ዝርያዎችን ችግኝ ጣቢያ ላይ አፍልቶ የሚያጋጥሙ የችግኝ መጠን ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ መንገዶች በመተግበር ላይ ናቸው፡፡
ይህ የሙከራ ትግበራ በዋናነት ትኩረት አድርጎ የሚሰራው በአገር በቀል የዛፍ ዝርያዎች ላይ ሲሆን የዛፍ ዝርያዎቹን እንዴት መጠበቅ እንዳለበት እና የደን ሽፋንን እንዴት መጨመር እንደሚቻል በጥናት የተደገፈ ስራ ለመስራት ታላሚ ያደረገ ነው።
ስልጠናውን ሲሰጡ ያገኘናቸው የቦኩ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ዶክተር ሃፍቴ መብርሃተን “የሃበሻ ጥድ በተፈጥሮው የመብቀል አቅሙ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ እና ደኑ ባለበት አካባቢ በተፈጥሮ የመተካት ሂደቱ አነስተኛ በመሆኑ በቁርጥራጭ (Cutting) የማባዛት ስልጠና ባለድርሻዎች ባሳተፈ መንገድ እየሰጠን ነው” ብለዋል ።
ዶክተር ሃፍቴ መብርሃተን አክለው እንደገለፁት “በቁርጥራጭ የማባዛት ስራውን ለማሳካት ቁርጥራጭ የሃበሻ ጥድን በመትከል ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ ሙከራዎች እየተደረጉ ሲሆን በሶስት ወራት የሙከራ ትግበራ ሂደት ላይ የዕድገት ሆርሞን በመጠቀም ዕድገቱ ያስገኘውን ውጤት ለማወቅ እንዲያስችል እየተሰራ መሆኑን” አስረድተዋል፡፡
ጥናቱ ለማከናውን በሀገራችን ውስጥ ከተመረጡ ከሀረር፣ ከጉራጌ ቆጠር ገድራ፣ከደብረብርሃን እና ከጉለሌ አካባቢዎች ከተሰበሰቡ ዘሮችና እፅዋት ናሙና ተወስዶ ጥናት እየተደረገባቸው ነው፡፡ ጥናቱም ቀጣይነት ባለው መልኩ እነዚህ የተሻሻሉ የእፅዋት ዝርያዎችን አያያዝ እና የደን አስተዳደር ስልቶችን በመጠቀም ለግለሰቦች፣ ለድርጅቶች እና ለመንግስት አካላት ተደራሽ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ደን ልማት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ የደን ልማትና ምርምር ማዕከል የተፈጥሮ ሃብትና የአየር ንብረት ለውጥ ምርምር ተመራማሪ አቶ ነስሩ ሀሰን እንዳሉት “ስልጠናው እየተሰጠ ያለው በአዲስ አበባ እና በዙሪያው ለሚገኙ የግል እና የመንግስት ችግኝ ጣቢያ አስተባበሪዎች መሆኑን ገልፀው የሃበሻ ጥድን በቁርጥራጭ ለማልማት የበለጠ የእውቀት ሽግግር እንዲያገኙ ታስቦ የተዘጋጀ ነው” ብለዋል፡፡
የስልጠናው ተሳታፊዎች ባገኙት ስልጠና ታግዘው በየአካባቢያቸው የሃበሻ ጥድን በቁርጥራጭ በማባዛት ዝርያው በሀገራችን እንዲስፋፋ በሚደረገው ጥረት ሁሉ የበኩላቸውን ለማበርከት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡
