የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩም የግብርና ምርታማነትን በማገዝ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ያስገኘ ዓለም አቀፍ ተነሳሽነት ነው።
በኢትዮጵያ ደን ልማት የተፈጥሮ ደን መሪ ሥራ አስፈጻሚ ካብታሙ ግርማ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ደን የአካባቢ መራቆትና የሥነ-ምኅዳር ደህንነትን በመጠበቅ ለግብርና ምርታማነት ጉልህ ጠቀሜታ አለው።
የደን ሽፋን ዕድገትም አየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቀነስ ብርቅዬ እንስሳትና የብዝኅ ሕይወት ደኅንነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የመደመር መንግሥት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለደን ልማት የሰጠው ትኩረት የአካባቢ ተጽዕኖ ውጤታማነትን በማሻሻል ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ዜጎች በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ተያያዥ የልማት መስኮች የሚሰማሩበትን ዕድል በመፍጠር ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ እያስገኘ መሆኑን አንስተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጭነት በ2011 ዓ.ም. የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራም 17 ነጥብ 2 በመቶ የነበረውን ደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማሳደጉን አስታውሰዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የደን ጥበቃ ውጤታማነትን በማላቅ የተስተካከለ ሥነ-ምኅዳርና የብዝኅ ሕይወት እንዲፈጠር እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በተለይም የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረግ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ እፅዋት ልማትን በማስፋፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መሠረት እየጣለ መሆኑን አብራርተዋል።
የህብረተሰቡን የደን ጥበቃና እንክብካቤ ባህል በማሻሻል የደን አስተዳደር ሥርዓት ውጤታማነትን ማሳደግ የሚያስችል አቅም መፈጠሩንም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ደን ልማትም የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ፣ የደን ሀብት በዘላቂነት እንዲጠበቅና እንዲለማ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በተጨማሪም የደን ውጤቶች ምርታማነትን በማሻሻል የደን ሀብት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚነትን በማላቅ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል
