ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ለ2018 በጀት ዓመት “የአረንጓዴ አሻራ ብሄራዊ መርሀ ግብር” የተከላ ቦታ ልየታና ዝግጅት

ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ለ2018 በጀት ዓመት “የአረንጓዴ አሻራ ብሄራዊ መርሀ ግብር” የተከላ ቦታ ልየታና ዝግጅት፣ የችግኝ ማፍላትና ሌሎች ግብአቶች ማሟላት ዝግጅት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ደን ልማት ገለፀ።
ሰኔ/2018 ዓ፣ም
ሲዳማ ክልል፣ ሸበዲኖ ወረዳ
*************®********
የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በውጤታማነት እየተተገበረ ይገኛል። በዚህ ትግበራም በሚሊዮኖች ሄክታር የተራቆተ መሬት አገግሟል፣ የደን ሽፋናችን ጨምሯል፣ ለሚሊዮን ዜጎችም የስራ እድል ተፈጥሯል፣ የአፈር መሸርሸርና መከላት ቀንሷል፣ የዓየር ንብረት ለውጥን አሉታዊ ተፅኖ ለመቋቋምም የራሱን ድርሻ አበርክቷል፤ ለዝናብና ለከርሰ ምድር ውሀ ሀብት ግኝታችንን መጎልበትም አሰተዋፅኦ አድርጓል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከነዚህ ፋይዳዎች በተጨማሪም ለምግብነት የሚውሉ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንሰሳት መኖ፤ ለአካባቢ ጥበቃና ለከተሞች ውበት ፋይዳ ያላቸው ችግኞችን በማፍላትና በመትከል ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ፣ ተጨማሪ ገቢ ለማስገኘትና አካባቢን ለመጠበቅ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን አበርክቷል።
በኢትዮጵያ ደን ልማት የአረንጓዴ አሻራና ሰው ሰራሽ ደን መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ አበሩ ጠና የ2018 በጀት ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በመስክ ለመመለልከትና ድጋፍ ለማድረግ ወደ ኦሮሚያና ሲዳማ ክልሎች ተገኝተን ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት “የአረንጓዴ አሻራ ብሄራዊ መርሀ ግብር ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ በርካታ ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀው በተለይ ይህ ስራ ህዝባዊ መሠረት ኖሮትና ባህል ሆኖ እንዲቀጥል የተፈጠረው ግንዛቤና መነሳሳት እንዲሁመ ከዘርፉ የሚገኘውን ጠቀሜታ በተግባር መረጋገጥ መጀመሩ ትልቅ ውጤት ነው” ብለዋል።
እንደ አቶ አበሩ ገለፃ ከአረንጓዴ አሻራ ብሄራዊ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ወደ ተግባር ከመግባቱ በፊት እ.አ.አ. በ2016 በዓለም አቀፍ የሀብት ኢንስቲትዩት(WRI) በተጠና ጥናት በኢትዮጵያ 54 ሚሊዮን ሄክታር የተጎዳ መሬት መኖሩንና ከዚህ ውስጥ ደግሞ 11 ሚሊየኑ ሄክታር አፋጣኝ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት ጥናቱ አመላክቷል። በመሆኑም ሀገራችን የገባቻቸውን አለማቀፍና አህጉር አቀፍ የአካባቢ ስምምነቶች ታሳቢ በማድረግ፣ ሀገራዊ እድገት ለማምጣት ለይተን የምንተገብራቸው ሀገር በቀል የእድገት አማራጮቻችን እንዲፋጠኑና የምግብ ዋስትናችንን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ዘርፉ ያለውን ሁሉን አቀፍ ጠቀሜታ በመረዳት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን “የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን ሀሳብ በማመንጨትና ለትግበራውም ግንባር ቀደም አመራር በመስጠት እንዲሁም ጉዳዩ ከሀገር አልፎ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ አጀንዳ እንዲሆን አበክረው በመግለፅ በሀገራችን የመጀመሪያ የሚባል ስኬትን ማስመዝገብ ችለናል።
በዘንድሮው የክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ8 ቢሊዮን በላይ የተለያየ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች የተፈሉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 60% የሚሆኑት የምግብ ዋስትናን ሊያረጋግጡ የሚችሉ የአትክልት፣ ፍራፍሬና የሚበሉ የዛፍ ዝርያዎች ናቸው ተብሏል።
በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ “ጥብቅና የተመናመኑ ደኖች ልማትና ጥበቃ” ባለሙያ የሆኑት አቶ ብዙነህ አበራ በመስክ ስራችን ወቅት እንደነገሩን “በክልሉ ባለፉት ሰባት ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተለያየ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን ገልፀው በአማከይ 85% መፅደቁን ነግረውናል። ባለሞያው አክለው በዘንድሮው የክረምት ወራት በክልሉ 320 ሚሊዮን የደንና የተለያየ ጠቀሜታ የሚያሰገኙ ችግኞች ለተከላ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀውልናል።
በክልሉ ሸበዲኖ ወረዳ ፉሮራ ቀበሌ ተገኝተን እንዳየነው በ2.5 ሄክታር መሬት ላይም ሀንሰንና ኢንቲን የተባሉ የተሻሻሉ የአቮካዶ ዝርያዎችን በማምረትና ለአካባቢው ማህበረሰብ እያቀረቡ መሆኑን አርሶ አደር ረህመት ደምሴ ገልፃልናለች። እንደ ወ/ሮ ራህመት ገለፃ ወደ ተሻሻለ አቮካዶ ልማት በ2012 ዓ.ም ሲገቡ በ50 ቾግኞች ሥራ መጀመራቸውን ገልፀው ለስራው መነሻ ሀሳብ የሆናቸውም “ሀገራዊው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር” መሆኑን ገልፀውልናል።
ወ/ሮ ረህመት በአሁኑ ወቅት መስኖንም በመጠቀም ጭምር በዓመት ሁለት ጊዜ የሚያመርቱትን አቮካዶ ይርጋለም አግሮ ፕሮሰሲንግ ፋብሪካ በግብአትነት እንደሚረከባቸው ገልፀው በዚህም የኢኮኖሚ አቅማቸው እያደገ መምጣቱን ነግረውናል።

ተዛማጅ ልጥፎች